ሳዑዲ አረቢያና ሶፍት ባንክ የዓለማችን ግዙፉን የፀሃይ የኃይል ማመንጫ በ200 ቢሊየን ዶላር ሊገነቡ ነው

Home of best apps

ሳዑዲ አረቢያና ሶፍት ባንክ የዓለማችን ግዙፉን የፀሃይ የኃይል ማመንጫ በ200 ቢሊየን ዶላር ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሳኡዲው ልዑል መሃመድ ቢን ሰልማን ሶፍት ባንክና ሳኡዲ አረቢያ በ200 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከፀሃይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ (ሶላር) ሊገነቡ መሆኑን አስታወቁ፡፡

በአሜሪካ የሶስት ሳምንት ጉብኝት ላይ የሚገኙት ልዑል ቢን ሰልማን እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት በኒውዮርክ ነው፡፡

ፕሮጀክቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት አብረዋቸው የነበሩት የጃፓኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ማሳዮሺ ሰን የመነሻ ኢንቨስትመንቱ የ5 ቢሊየን ዶላር ነው ብለዋል፡፡

ሁለቱ አካላት በትላንትናው ዕለት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ፕሮጀክቱ ከአስር ዓመታት በላይ እንደሚፈጅ የተነገረ ሲሆን÷ እንደ አውሮፓውያን ዘመን ቀመር በ2030 ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

ስራ አስፈጻሚው ፕሮጀክቱ 100 ሺህ የስራ ዕድሎችን ይፈጥራል ያሉ ሲሆን÷ አገሪቷ ለኃይል አቅርቦት የምታወጣውን 40 ቢሊየን ዶላር እንድትቆጥብ ያስችላታል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የአገሪቷን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርትን በ12 ቢሊየን ዶላር ሊያሳድግ እንደሚችልም ተንብየዋል፡፡

ፕሮጀክቱ 200 ጊጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ የተገለጸ ሲሆን÷ ለ20 ቢሊየን አምፖሎች ኃይል ማቅረብ ይቻለዋል ነው የተባለው፡፡

ልዑል መሃመድ ቢን ሰልማን ሳኡዲን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ ባለፉት ጊዜያት ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎችን ማድረገቸው የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

ምንጭ፦ሲ.ኤን.ኤን
ተተርጉሞ የተጫነው፦ በአብረሃም ፈቀደ