ዩ ቲዩብ፣ ፌስ ቡክ እና አፕል የአሌክስ ጆንስን የሴራ ንድፈ ሃሳብ ስራዎች ከገጻቸው አገዱ

Home of best apps

ዩ ቲዩብ፣ ፌስ ቡክ እና አፕል የአሌክስ ጆንስን የሴራ ንድፈ ሃሳብ ስራዎች ከገጻቸው አገዱ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶስት የማህበራዊ ትስስር ገጾች አወዛጋቢው የሴራ ንድፈ ሃሳብ አዘጋጅና አቅራቢ አሌክስ ጆንስ ስራዎች ላይ እገዳ ጥለዋል።

ፌስ ቡክ፣ ዩ ቲዩብ እና አፕል ግሰለቡ በቶክ ሾው ፕሮግራሞቹ በማዘጋጀት በገጾቹ ላይ የሚለጥፋቸውን ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማገዳቸውን አስታውቀዋል።

ለዚህ ደግሞ አሌክስ ጆንስ የሚያነሳቸው ሃሳቦች እጅግ አወዛጋቢና የኩባንያዎቹን የማህበራዊ ሚዲያ መተዳደሪያ ህግ የሚጣረስ መሆኑን ገልጸዋል።

ፌስ ቡክ ግለሰቡ ከሚኖርበት ማህበረሰብ ባፈነገጠ መልኩ መቃቃርን የሚፈጥሩና የጥላቻ ንግግሮች ያሉባቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ከገጹ ላይ ማጥፋቱንም ነው ያስታወቀው።

ከዚህ ባለፈም ግለሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በማህበረሰቡ መካከል ከፍ ያለ ቅራኔ እና ግጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሃሳቦችን የያዙ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መልቀቁንም ነው ሶስቱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የገለጹት።

ይህን ተከትሎም ፌስ ቡክ በትናንትናው እለት በግለሰቡ የተዘጋጀና የጥላቻ ንግግር ያዘለ ነው ያለውን ተንቀሳቃሽ ምስል ማስወገዱን ይፋ አድርጓል።

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2001 መስከረም ወር ላይ በኒው ዮርክ መንትያ ህንጻዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአሜሪካ የተቀነባበረ ነው የሚል መላ ምት ያቀርባል።

በተጨማሪም በአሜሪካ በፈረንጆቹ 2012 ኮኔክቲከት ኒውታዎን በሚገኘው ሳንዲ ሁክ ትምህርት ቤት የተፈጸመውን ግድያም የይስሙላ ነው በሚል በሚያቀርበው ቶክ ሾው ላይ በተደጋጋሚ አቅርቧል።

በወቅቱ በዚህ ትምህርት ቤት አንድ ታዳጊ በፈጸመው ጥቃት 20 የትምህርት ቤት ጓደኞቹን ህይዎት መቅጠፉ ይታወሳል።

ይህ ያበሳጫቸው የተጎጅ ቤተሰቦች እንዲሁም ከኒው ዮርኩ ጥቃት ጋር በተያያዘ ባቀረበው መላ ምት በርካቶች ክፉኛ ኮንነውታል።

እነዚህን ጨምሮ ወደ አውሮፓና ሌሎች ሃገራት የሚገቡ ሙስሊም ስደተኞችን በተመለከተ በሚያነሳቸው ሃሳቦች ተቃውሞን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

መሰል ይዘት ያላቸው የተንቀሳቃሽ ምስሎቹም ከማህበራዊ የትስስር ገጾች እንዲጠፉ ተደርገዋል።

ፌስ ቡክ እነዚህ መረጃዎች ከገጹ ላይ ሲያግድ አፕል በበኩሉ በአይ ቲዩንስ በኩል ለተከታታዮቹ ከሚደርሱ 6 ተንቀሳቃሽ ምስሎች መካከል አምስቱን አግጃለሁ ብሏል።

ይሁን እንጅ የአሁኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾቹ እርምጃ የመናገር ነጻነትን የተጻረረ ነው በሚል ወቀሳ እየቀረበበት ይገኛል።

በርካቶችም አሁን የተጀመረው አካሄድ የሃገሪቱን የሚዲያ ነጻነት ህግ የሚጋፋ ነው በሚል በድጋሚ እንዲጤን ሃሳብ አቅርበዋል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *