ኡበር አሽከርካሪ አልባ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ማምረት ሊያቆም ነው

Home of best apps

ኡበር አሽከርካሪ አልባ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ማምረት ሊያቆም ነው

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 24 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኡበር አሽከርካሪ አልባ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ማምረት ሊያቆም መሆኑ ተሰምቷል።

ኩባንያው በፈረንጆቹ 2016 በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ አሽከርካሪ አልባ የሆኑ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ማምረት መጀመሩ ይታወሳል።

ኡበር ይህን አገልግሎት የጀመረው የተቀላጠፈና ፈጣን የጭነት ማመላለስ አገልግሎት ለመስጠት በማለም መሆኑ ይነገራል።

አሁን ላይ ግን ከዚህ አገልግሎት በመውጣት ሙሉ በሙሉ በአነስተኛ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ማምረት ላይ ትኩረት ለማድረግ ማሰቡን ነው የገለጸው።

ኡበር በዘርፉ በሚሰጠው አገልግሎት ቀዳሚ ጀማሪ በመሆን ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፉ ይነገራል።

ይሁን እንጅ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በተከሰቱ አደጋዎች ሳቢያ ወቀሳ ሲቀርብበትም ቆይቷል።

ከዚህ ውስጥ በአሜሪካ አሪዞና የ49 አመት ጎልማሳ መንገድ ሲያቋርጡ በደረሰባቸው አደጋ ሳቢያ ህይዎታቸው አልፏል።

ይህን ተከትሎም ኩባንያው ባለፈው መጋቢት ወር በአሜሪካ ያደርጋቸው የነበሩ የአሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪ የጎዳና ላይ ሙከራዎች ማቋረጡን ገልጾም ነበር።

በርካታ ተሽከርካሪዎቹ ከጎዳና ላይ ሙከራ ይልቅ ተገጣጥመው ለመቀመጥ ተገደዋል።

በርካታ ኩባንያዎችም የወደፊቱን የትራንስፖርት አገልግሎት በአሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ለማድረግ ከወዲሁ የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛል።

ባለሙያዎች ግን ይህን ዘርፍ ወደ ስራ ከማስገባት በፊት ቢያንስ አደጋዎችን መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጅ ቀደም ብሎ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና ሬውተርስ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *