ዩ ቲዩብ አላስፈላጊ ይዘት ያላቸውን 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አስወገደ

Home of best apps

ዩ ቲዩብ አላስፈላጊ ይዘት ያላቸውን 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አስወገደ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 16 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩ ቲዩብ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት አላስፈላጊ ይዘት ያላቸውን 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጥፋቱን አስታወቀ።

ኩባንያው በፈረንጆቹ 2017 ሶስተኛ ሩብ አመት የስራ አፈጻጸሙን የተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል።

በሪፖርቱ ላይም ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር ድረስ የኩባንያውን ህግና ደንብ የተላለፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች (ቪዲዮ) ማጥፋቱን ነው ያስታወቀው።

ለዚህ ደግሞ ከተጠቃሚዎች የደረሰውን አስተያየት መሰረት በማድረግ መሆኑንም ገልጿል።

ካስወገዳቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ውስጥ ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፥ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን ከሚሆኑ ተከታታዮቹ ጥቆማ እንደደረሰው ነው የገለጸው።

4 ነጥብ 7 ሚሊየን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ደግሞ በገጹ ላይ የጥላቻ ይዘት ያላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተሰራጭተዋል በሚል ለኩባንያው ሪፖርት አድርገዋል።

አብዛኛው ጥቆማ እና ቅሬታም ከህንድ፣ አሜሪካ ወይም ብራዚል የደረሰው መሆኑም ነው የተነገረው።

ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ የተወገዱት ከኩባንያው ህግና ደንብ ውጭ በሆነ መልኩ፥ ወሲብ ቀስቃሽና የጥላቻ ይዘት ያላቸው ሆነው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈ ግን ኩባንያው ከባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ የተወገደ ወይም እንዲጠፋ የተደረገ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሌለውም አስታውቋል።

እንደ ኩባንያው መግለጫ ከጠፉት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ውስጥ 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ያክሉ፥ ሰዎች ጋር ሳይደርሱ ኩባንያው ባዘጋጀው መሳሪያ የተለዩ ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም 76 በመቶ ያክሉ ለተጠቃሚዎች ሳይደርሱ እንዲጠፉ ተደርጓልም ነው ያለው ኩባንያው።

ኩባንያው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለእይታ መቅረብ የማይገባቸውና ወሲብ ቀስቃሽ፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ ፕሮፓጋንዳ እና አላስፈላጊ መልዕክቶች ሲተላለፉ በአግባቡ መቆጣጠር አልቻለም በሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

ከዚህ ባለፈም ዘረኝነት የሚንጸባረቅባቸውና የአፍቃሪ ነጭ እና ናዚ ማስታወቂያዎችም በገጹ ላይ በስፋት ይሰራጫሉ በሚልም ወቀሳ ቀርቦበታል።

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *