ህንድ ፌስ ቡክን ጨምሮ መልዕክት መላላኪያ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲዘጉላት ጠየቀች

Home of best apps

ህንድ ፌስ ቡክን ጨምሮ መልዕክት መላላኪያ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲዘጉላት ጠየቀች

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድ የቴሌኮም ዘርፍ ባለሙያዎቿ የተወሰኑ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾችና መተግበሪያዎችን እንዲያግዱላት እየጠየቀች ነው።


የህንድ መንግስት የሃገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ባለሙያዎች ፌስ ቡክ እና በኩባንያው የሚተዳደሩትን ዋትስ አፕን እና ኢንስታግራምን ማገድና አገልግሎት እንዳይሰጡ ማቋረጥ የሚችሉበትን መንገድ ይፈልጉ ዘንድ ጠይቋል ነው የተባለው።

ሬውተርስ ጉዳዩን በተመለከተ የሚገልጽ መረጃ አገኘሁ ብሎ ባወጣው ዘገባ ህንድ፥ ፌስ ቡክና በስሩ የሚያስተዳድራቸውን መልዕክትና ምስል መላላኪያ መተግበሪያዎች አገልግሎት መስጠት የማይችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት የባለሙያዎቹን ድጋፍ ጠይቃለች ብሏል።

ለዚህ ደግሞ መልዕክት መላላኪያዎቹ በሃገሬው ሰዎች ዘንድ ባልተገባ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው የሚል ምክንያት መንግስት አቅርቧል ነው የተባለው።

ምክንያቱም ተጠቃሚዎች ፌስ ቡክንም ሆነ ሌሎችን መተግበሪያዎች የተሳሳተ መረጃ እየተቀባበሉበት ነው የሚል ቅሬታን አቅርቧል።

ይህ ደግሞ በሃገሪቱ ለነውጥና ብጥብጥ ምክንያት እየሆነ ነው በሚል እገዳውን እውን ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ እየፈለገ ነው ብሏል ዘገባው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም ዋትስ አፕ በህንድ ባለስልጣናት ዘንድ በጥሩ መልኩ አይታይም።

መተግበሪያው ለብጥብጥና አመፅ የሚዳርጉ መልክዕቶች መላላኪያ ሆኗል በሚል ባለስልጣናቱ በአስቸኳይ ይዘጋ ዘንድ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሌላኛው የመልዕክት መላላኪያ የሆነው ቴሌግራምም በህንድ እንዲቋረጥ የሃገሪቱ መንግስት ባለሙያዎቹን እገዛ ጠይቋል።

የሃገሪቱን መንግስት ጥያቄ ተከትሎ አሁን ላይ ዋትስ አፕ ተጠቃሚዎቹ ጠቃሚ የመረጃ ልውውጥ ብቻ ያደርጉ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማስታወቂያዎችን መልቀቅ መጀመሩን ገልጿል።

ማስታወቂያው ተጠቃሚዎቹ መልዕክት በሚላላኩበት ወቅት አላስፈላጊና ጠብ አጫሪ የሆኑ መልዕክቶችን እንዳይላላኩ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ነው የተነገረው።

የአሁኑ የህንድ መንግስት ጥያቄ በሃገሪቱ ካለው ሁኔታ አንጻር የሃገሪቱን ደህነነት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ።

ምንጭ፦ ሬውተርስ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *